Post by Yoseph bekele Josi

--

#USA #IRAN በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ዳግም ወታደራዊ ግጭት ተቀሰቀሰ ፤ ሀገራቱ ለውጥረቱ እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ነው። የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ፥ ኢራን 'M/V Ever Lovely' በተሰኘችው የንግድ መርከብ ላይ የድሮን ጥቃት በመሰንዘር በሀገራቱ መካከል የነበረውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሳለች ብሏል። አሜሪካ ለዚህ ጥቃት ምላሽ በሚሆን መልኩ በኢራን የሚሳኤል ማከማቻዎች፣ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጣቢያዎች እና የራዳር መሠረተ-ልማቶች ላይ ተከታታይ የአየር ድብደባ መፈጸሟን ይፋ አድርጋለች። ኢራን በበኩሏ የቀረበባትን የአሜሪካን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጋለች። የቴህራን ባለስልጣናት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዳልጣሱ በመግለጽ፣ ይልቁኑ "አሜሪካ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን መጀመሪያ የጣሱ አካላት ናቸው" ሲሉ የተገላቢጦሽ ክስ ሰንዝረዋል። የሀገሪቱ ፓርላማ የጸጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ኢብራሂም አዚዚ የአሜሪካን ጥቃት " ግዴለሽነት የተሞላበት የተኩስ አቁም ጥሰት " ሲሉ የኮነኑ ሲሆን፣ ድርጊቱ ትራምፕ ለድርድርም ሆነ ለተኩስ አቁም መርሆዎች ቁርጠኝነት እንደሌላቸው ያሳየ ነው ብለዋል። አክለውም ይህ ጥሰት ለአሜሪካ ውድቀትንና ጸጸትን እንደሚያስከትል ገልጸው "የወቀሳ ጨዋታው ከእንግዲህ አይሰራም" ሲሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም የኢራን ኢስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጦር (IRGC) ባወጣው መግለጫ በአሜሪካ ሲሪክ ደሴት ላይ ተፈጸመ ያለውም ጥቃት የባህርና የአየር ኃይሉ ማክሸፍ እንደቻሉ አስታውቋል። ድርጊቱ "ያለ ምላሽ አይቀርም" ያለ ሲሆን ተገቢ በሆነ ጊዜና ቦታ ፈጣንና ወሳኝ ምላሽ ይሰጣል ሲል አጠንቅቋል። አሁን ላይ ሁለቱም ወገኖች ለተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት አንዳቸው ሌላውን ተጠያቂ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህ አዲስ ወታደራዊ ፍጥጫ ሁለቱ ሀገራት በቅርቡ በስዊዘርላንድ ያደረጉትን የዲፕሎማሲ ጥረት አደጋ ላይ ጥሎታል። በሀገራቱ መካከል ምንም ዓይነት የመጨረሻ እና ቋሚ የሰላም ስምምነት ያልተፈረመ ሲሆን፣ በስዊዘርላንድ ተካሂዶ የነበረው ውይይት የጊዜያዊ ተኩስ አቁምና እሱንም ተከትሎ ለቀጣይ ድርድሮች መነሻ የሚሆን ፍኖተ-ካርታ ለማዘጋጀት የተደረገ ነበር። ያ የድርድር ማዕቀፍ ፦ - ቀጣናዊ ጸጥታን፣ - የማዕቀብ ጉዳይን፣ - የኢራንን የኑክሌር ፕሮግራም የተመለከቱ አጀንዳዎችን በሂደት ለመፍታት ያለመ ነበር። ውይይቱን ተከትሎ የሆርሙዝ ሰርጥ በተወስነ መልኩ መረጋጋት ታይቶበት የነበረ ሲሆን የነዳጅ ዋጋም አሽቆልቁሎ ነበር። በዛሬው ዕለት በሁለቱም ወገኖች የተሰነዘሩት ክሶች እና የታዩት ወታደራዊ እርምጃዎች ጊዜያዊ የተኩስ አቁሙን አደጋ ላይ የጣለና ቀጠናውን ዳግም ወደ ከፍተኛ ስጋት የከተተ ሆኗል። ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ/ም @tikvahethiopia

Post content