Post by Seble Asefa
Consultant and Attorney at Law, Election Observer and Gender Equality Specialist , Ethiopia.
በፍቺ ሂደት ለአንደኛው ለባል/ሚስት ከሌላኛው ንብረት ተቀንሶ ካሳ እንዲከፈል የሚወሰንባቸው 3 ሁኔታዎች! Seble Asefa በፍቺ ሂደት ፍ/ቤቶች ለአንደኛው ተጋቢ ካሳ ሊወሰን እንደሚችል በኢፊዲሪ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ አንደኛው ተጋቢ በሚያቀርበው ጥያቄ አማካኝነት የቤተሰብ ችሎቶች ካሳ የሚወስኑበት አግባብ ከታች በተመለከቱት 3 ሁኔታዎች (Scenarios) ነው፡፡ 1. የጋራ ንብረታችንን ወይም የግል ንብረቴን እንዲያስተዳድር የሰጠሁትን ውክልና ያለአግባብ ተጠቅሟል የሚያሰኝ ሁኔታ ሲኖር ነው፡፡ ባል ወይም ሚስት በጋብቻ ያፈሩትን ንብረት እንዲያስተዳድሩ በእምነት የተሰጣቸውን ስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም፣ በብልሹ አስተዳደር ምክንያት ወይም ካሳ ጠያቂውን ባል/ሚስት በማታለል በሌላኛው የንብረት መብት ላይ ጉዳት ካደረሱ የሚወሰን የካሳ አይነት ነው፡፡ (አንቀጽ 87 (1)) በተጨማሪም አንድኛው ተጋቢ ለምሳሌ ሚስት ከጋብቻ በፊት ያፈራችው ቤት፣ ድርጅት፣ መኪና ወዘተ ቢኖርና ባል እንዲያስተዳድርላት ውክልና ከሰጠችው ንብረቱን በአግባቡ በእምነት የማስተዳደር ሀላፊነት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ውክልና የሰጠሁበትን ንብረት በብልሹ አስተዳደር በተንኮልና ማታለል ጉዳት አድርሶበታል የሚያስብል ተግባር ከፈጸመ ካሳ መጠየቅ ትችላለች፡፡ ከድርጅቱ ንብረቱ ማግኘት ያለብኝን ጥቅም እንደላገኝ አታሎኛል ካለችም በፍቺው ሂደት ይህን በባሏ አማካኝነት የደረሰን ጉዳት ከግምት ከቶ ፍ/ቤቱ በንብረት ክፍፍል ወቅት ለባሏ ከሚደርሰው 50 በመቶ ተቀንሶ በካሳ መልክ እንዲከፈላት ልትጠይቅ ትችላለች፡፡ የቤተሰብ ችሎቶች እንዲህ ያሉ የካሳ ጥያቄዎችን ተቀብለው በማስረጃ አንጥረው ሊወስኑ እንደሚገባ የቤተሰብ ህጋችን ደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ የጋራ ንብረትን ወይም በባል/ሚስት የግል ንብረት ላይ የተከወለው ተጋቢ በንብረት ላይ ጉዳት አድርል በሚል መነሻ በፍቺ ንብረት ክፍፍል ወቅት ካሳ ሊጠየቅ የሚችለው ድርጊቱ ፍቺ አቤቱታው ከመቅረቡ ከ5 አመት ወደዚህ የተፈጸመ ከሆነ ነው፡፡ (አንቀጽ 87 (2)) 2. ያለአግባብ መበልጸግ ሲኖር፡- ለምሳሌ ሚስት የግል ንብረት ድርጅት ቤት ቢኖራትና ባልየው ያለአግባብ ከዚህ ድርጅት ቤት ንብረት ተጠቅሟል ፡ ራሱን አበልጽጓል የሚባልበት ሁኔታ ካለ ሚስት በፍቺ የጋራ ንብረት ክፍፍል ወቅት በዚህ የባልየው ተግባር ምክንያት የደረሰባት ጉዳት ከባልየው 50 በመቶ ድርሻ ላይ ተቀንሶ እንድትካስ ልትጠይቅ ትችላለች፡፡ በተጨማሪም ባልየው የሚስቱን የግል ንብረት ያለአግባብ በመጠቀሙ የጋራ ሀብታቸው ያለአግባብ መበልጸጉን ማስረዳት ከቻለች ሚስት ይህንን ካሳ ልትጠይቅ ትችላለች፡፡ የቤተሰብ ችሎቶች መሰል የካሳ ጥያቄ የሚያቀርብ ሚስት/ባል በበቂ ማስረጃ የተደገፈ የካሳ ጥያቄ ሲቀርብ ለሁለቱም ከሚደርስ የባልና ሚስት የጋራ ንብረት ክፍፍል 50 በመቶ ድርሻ ያለአግባብ መበልጸጉ ለጎዳው ተጋቢ ካሳ ይወስናሉ፡፡ 3. ለፍቺ ምክንያት የሆነውን ጥፋት የፈጸመ ባል/ሚስት ላይ ስለሚወሰን ካሳ፡- ይህ አይነቱ የካሳ ጥያቄ ለፍቺው ምክንያት የሆነው በባል ወይም ሚስት የተፈጸመ በደል አመንዝራነት ድብደባ እና መሰል ተግባር ከሆነ ተበዳዩ ካሳ ሊጠየቅ እንደሚችልና የቤተሰብ ችሎቶቸ ለፍትህ አስፈላጊ ነው ብለው ሲያምኑ በዳዩ ከሚያገኘው የጋራ ንብረት ክፍፍል ድርሻ ተቀንሶ ለተበዳዩ በካሳ መልክ እንዲከፈል ሊወስኑ እንደሚችሉ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 84 ተመልክቶ ይገኛል፡፡፡ Legal Eagles Law Firm LLP / Ethiopian Corporate & Investment Lawyers #lawfirm #lawyers #EthiopianLaw #ethiopianlawyer #lawfirminethiopia #law #ForeignDirectInvestment #